Skip to content

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በድሬዳዋ ከተማ ለሴቶች ያዘጋጀው የሦስት ቀናት የአቅም ግንባታ መድረክ ተጠናቀቀ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ባለው ሁኔታ መሳተፍ እንዲችሉ ለማድረግ በድሬዳዋ ከተማ ከመጋቢት 06-08 ቀን 2015 ዓ.ም ለሦስት ቀናትያዘጋጀው የአቅም ግንባታ መድረክ ተጠናቀቀ።

በምክክር መድረኩ የመጀመሪያ ቀን ላይ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ  ከሴቶች ፌዴሬሽን፣ ሴት አካል ጉዳተኞች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ የቤት እመቤቶች፣ ሴት የእድር አባላት፣ የሲቪክ ማኅበራት ሴት አባላት፣ የሕግ ባለሞያ ሴቶች፣ ሴት ወጣቶች እና ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ለተውጣጡ 149 ሴቶች፣ ሁለተኛ ቀን ከገጠር ቀበሌዎች ልዩ፣ ልዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ 156 ሴቶች እንዲሁም ሦስተኛ ቀን የመስተዳድር አካላትን ጨምሮ በተለያዩ የሞያ መስኮች የተሰማሩ 50 ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የሀገራዊ ምክክር ምንነት፣  ሀገራዊ ምክክር ከድርድር፣ ሽምግልና እና እርቅ ጋር ያለው ልዩነት እና አንድነት እንዲሁም ሴቶች በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ የመሳተፍ እድል ቢገጥማቸው ሐሳባቸውን እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ የሚያስችል የአቅም ግንባታ በተመለከተ ለተሳታፊዎች በባለሞያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።  

ጥምረቱ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ የሴቶች ውክልና እና ተሳትፎ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት፣ በሀገር ደረጃ ሴቷ ድምጿ እንዲሰማ እና የራሷ አጀንዳ ያላት መሆኑ እንዲታወቅ የውትወታ ሥራ ይሠራል።

የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን በድሬዳዋ የተካሄደው መድረክ የሴቶች አቅም ግንባታ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ከሚያከናውናቸው መድረኮች የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመው፣ ዓላማው ሴቶች በምክክር ሂደቱ ውስጥ በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መድረኩ የተሳካ እንዲሆን በማስቻል ትብብር ላደረጉ የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ የድሬዳዋ ሲቪክ ማኅበራት ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ ጊዜያት ውስጥ በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *