Skip to content

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ (ጥምረት) ጠቅላላ ጉባኤ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም በሳሮ ማርያ ሆቴል ተካሂዷል።

የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለተገኙት የጥምረቱ አባላት እንኳን ደኅና መጣችኹ ብለዋል። አዳዲስ ለተቀላቀሉ አባላት ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሴቶችን መብቶች ለማስጠበቅ በሚሠሩ 22 የሲቪክ ማኅበራት መጋቢት 07 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ የተቋቋመ መሆኑ ገልጸዋል። በብሔራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና የሴቶችን ፍላጎቶች፣ ቀዳሚ ጉዳዮች እና ምኞቶች እውን እንዲሆኑ የማስቻል ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል። በአንድ ዓመት ገደማ ቆይታ ውስጥ ከ50 በላይ የሲቪክ ማኅበር አባላት ማፍራት መቻሉንም ጠቅሰዋል። የጠቅላላ ጉባኤው ዓላማ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ ጊዜያት እቅድ ውይይት የሚካሄድበት መሆኑን ተናግረዋል።

የጥምረቱ ሥራ አመራር ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ሰብሳቢ ሳባ ገብረመድኅን በበኩላቸው፣ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተገኙ አባላት ጥምረቱ የተቋቋመበትን በብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ የሴቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ እውን ለማድረግ እና አሁን ከደረሰበት ደረጃ የበለጠ እንዲጠናከር ከፉክክር ይልቅ በትብብር እንዲሠሩ አሳስበዋል።

በመቀጠልም የጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ከተነሡት ዋና፣ ዋና ነጥቦች መካከል የጥምረቱ ሥራ አመራር ግንቦት 2014 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሴቶች በብሔራዊ ምክሩ ሂደት ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ አብሮ ለመሥራት መግባባት ላይ መድረሱ ተጠቁሟል።

ባለፉት አንድ ዓመት ጊዜያት ውስጥ ጥምረቱ የተለያዩ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ማእከል በኩል የባለድርሻ አካላትን ገጽታ የሚያሳይ የጥናት ሰነድ፣ በትምራን በኩል የተግባቦት እና ቅስቀሳ ሰነድ፣ ተቋማዊ መለያ እና አርማ እንዲሁም የአባላት መተዳደሪያ ደንብ እንዲዘጋጁ አድርጓል።

ትምራን እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በጋራ ያዘጋጁት በሀገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የምክክር አመቻች አሠልጣኞች ሥልጠና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በተሰኘ አማካሪ ድርጅት አማካኝነት ጥር ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ላይ መሰጠቱ ተገልጿል።

የምክክር አመቻቾች የሥልጠና ሰነድ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በአፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ እና ሲዳምኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በኅትመት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ትምራን የጥምረቱ ሴክሬታሪያት በመሆኗ የምክረ ሐሳብ ሰነድ በማዘጋጀት ለጋሾች ዘንድ በመሄድ ለጥምረቱ ተግባራት በጀት የማፈላለግ ሥራዎች እያከናወነች መሆኑ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የጥምረቱ ሥራ አመራር አባላት የ14 ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ውይይት ማዘጋጀቷ ተጠቁሟል።

ለጋሽ በማፈላለግ ለጥምረቱ ሥራ አመራር በሰላም ግንባታ እና በብሔራዊ ምክክር ዙሪያ ያጠነጠነ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቷም ተነግሯል።

በተጨማሪም የጥምረቱ ሥራ አመራር ከሀገር ውጭ በኬንያ የሦስት ቀናት የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ማድረጓን ሪፖርቱ አትቷል።

ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የበጀት እጥረት፣ ለጋሽ ያላገኙ ተግባራት መኖር፣ አንዳንድ ሥራዎች አለመጀመር፣ በመላው ሀገሪቱ ምክክር የሚካሄድባቸው ስብስቦች ለመፍጠር አዳጋች ሁኔታዎች ማጋጠም፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት መኖር፣ ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እቅድ አንጻር የጥምረቱ ሥራ ዘግይቶ መጀመር እና ሌሎች ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል።

በመጨረሻም የጥምረቱ የቀጣይ ጊዜያት እቅዶች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፣ አስተያየቶች ተሰጥተው ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በጉባኤተኞች በኩል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የጥምረቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት የሆኑት እመቤት ኦላና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሴቶች ማኅበር እንዲሁም ማኅሌት አብርሃም ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ማእከል የጠቅላላ ጉባኤውን ውይይት በመምራት ተሳትፈዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከ30 በላይ የጥምረቱ አባል ሲቪክ ማኅበራት ተገኝተዋል።

የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሥራ አመራር ምክትል ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ሰብሳቢ ሌንሳ ቢየና የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። በዚሁ ወቅት ጥምረቱ የበለጠ እንዲያድግ ሁሉም አባል ማኅበራት ወደፊት መጥተው ሓላፊነት በመውሰድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ጥምረቱ በሰባት የሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት የሚመራ ሲሆን፣ ትምራን የጥምረቱ ሴክሬታሪያት ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *