ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የሴት አሠልጣኞች ሥልጠና በቢሾፍቱ ከተማ ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሥልጠናው ዓላማ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ሴቶች አሠልጣኞች እና አመቻቾች እንዲሆኑ ለማስቻል አቅም የመገንባት ተግባር ነው።
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ሰሎሞን ለክቡራን እንግዶች፣ ሠልጣኞች በተለይም ከትግራይ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጡ ተሳታፊዎች እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ሴቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲሳተፉ እና የሴቶች አጀንዳ እንዲያዝ ለማድረግ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መጋቢት 2014 ዓ.ም የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥምረቱ ከያዛቸው እቅዶች ውስጥ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው በሚደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች ዙሪያ ለሴቶች ግንዛቤ መፍጠር እና ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት ውይይት በማድረግ ፍላጎታቸውን መለየት ዋነኛው መሆኑንና ሥልጠናው ይህንን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የዚህ ሥልጠና ተሳታፊዎች በሁሉም ክልሎች በየደረጃው የሚደረጉ ውይይቶችን የማስተባበር እና ወደ ታች የማውረድ ሓላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም ሴቶች በሀገሪቱ ላይ የምናልመው ሰላም እንዲመጣ፣ የሀገራችንን እና የልጆቻችንን እድል እንድንወስን ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት እናምናለን፤ በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሴቶች ይህንን የሴቶች ሚና ለማጉላት ትልቅ ሓላፊነት የተጣለባችሁ ናችሁ ብለዋል።
በመቀጠል ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ሥራ አስኪያጅ እና የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሳባ ገ/መድኅን፣ በሀገራችን ሊካሄድ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ለሰላም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በመሆኑ የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም አሁንም ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ይህንን እውን ለማድረግ የተቋቋመ ነው፤ በመሆኑም ተቋማት በሴቶች ጉዳይ ላይ ተገቢውን ሚና ይጫወቱ ዘንድ ብሎም በመደበኛው አካሄድ ውሳኔ የማይሰጥባቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድኅን በበኩላቸው፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከትግራይ ክልል የመጡ ሠልጣኞች ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያው መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሴቶች የሰላም መሪ መሆናቸውን፣ እናት ጠንካራ ስትሆን ቤተሰብ፣ ሀገር ጠንካራ እንደምትሆን ተናግረዋል። ምክክሩ ለሁሉም አስፈላጊ ቢሆንም ሴቶች በአመቻችነት ተሳታፊ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል። ይህም ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አሻራ ማሳረፍ እንዲችሉ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዚህ ረገድ ምክክሩ ከተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲከናወን የማድረግ ሓላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊዎች የአካባቢውን ባሕል የሚያውቁ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፣ ከምክክር ሂደት በኋላ ምክረ ሐሳቦች እንደሚወጡ አመልክተዋል። ምክረ ሐሳቦቹም ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረጉ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክረ ሐሳቦች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ኮሚሽኑ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።
ሥልጠናውን ያስተባበሩት የጥምረቱ ጽ/ቤት የሆነችው ትምራን እና የጥምረቱ ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ የሆነችው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ናቸው።



