Skip to content

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የግብዓት ማሰባሰቢያ የመጨረሻ መድረኩን አካሄደ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የግብዓት ማሰባሰቢያ የመጨረሻ መድረኩን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይ የተሳታፊዎች ልየታ ስራ እንደሚያከናውንም ነው የተጠቆመው፡፡

ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር በመዘዋወር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በዛሬው እለት ደግሞ የግብዓት ማሰባሰቢያ የመጨረሻ መድረኩን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በመድረኩም የሃይማኖት አባቶች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የሀገራዊ ምክክር ጽንሰ ሀሳብ፣ ስለ አገራዊ ምክክር አስፈላጊነት፣ የምክክር ተሳታፊዎችን መለየት እንዲሁም አጀንዳ ማሰባሰብ አሰራርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን  ዋና ዋና ተግባራትን  አብራርተዋል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ክልሎች የተካሄዱ የውይይት መድረኮች ለኮሚሽኑ ቀጣይ ስራ እጅግ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኘባቸው እንደሆኑም ነው ያነሱት፡፡

በአዲስ አበባ ዛሬ የተካሄደውን የመጨረሻ የግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ  መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የተሳታፊዎች ልየታ እያንዳንዱ ማህበረሰብ አምኖበት የሚወክለውን የሚመርጥበት በመሆኑ ትልቁ የኮሚሽኑ ስራ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ካለው በጎ ሚና አንጻር የቀጣይ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው እንዲከናወኑ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

የምክክሩ ሂደት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም እንዲሁ፡፡

 የተሳታፊዎች ልየታ ሂደት በማን እንደሚከናወንም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

 የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በምላሻቸው፤ የተሳታፊዎች ልየታ ሂደት የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ባስገባና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡

 የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሃሳብና በፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት መድረኮችን እንዲያመቻች  የተቋቋመ ኮሚሽን ነው።

 ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የሂደት፣ የትግበራ እንዲሁም የትግበራና ክትትል ምዕራፎች ያሉት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ምዕራፉ ማጠቃለያ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

#ኢዜአ-ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *