Skip to content

የሴቶች አመራርነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ

ሴቶች በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለመሳተፍ ብዙ መሰናክሎች ያጋጥማቸዋል። መዋቅራዊ የሆኑ አግላይ ሕጎች እና ተቋማት ያለንበት ዘመን ድረስ ሴቶች ለውሳኔ ሰጭነት እንዳይወዳደሩ ማነቆዎች ሆነው ቀጥለዋል። በሴቶች ዘንድ የአቅም ውስንነት መኖር  ውጤታማ መሪዎች እንዳይሆኑ የሚያግዱ ከወንዶች ያነሰ የትምህርት፣ ትስስር እና ሀብት  የማግኘት ችግር እንዳለ ያሳያል።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ 2011 የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ አስመልክቶ ባስተላለፈው ውሳኔ፣ “በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ሴቶች አግላይ በሆኑ ሕጎች፣ ተግባራት እና ጾታዊ መድልኦ መኖር፣ ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት፣ ሕክምና የማግኘት እድል እና የሀብት ክፍፍል አናሳነት የተነሣ ከፖለቲካ ተሳትፎ በስፋት ተገልለው እንደሚገኙ አመልክቷል።  

ይህም ሆኖ አንዳንድ ሴቶች እነዚህን መሰናክሎች በጽናት ተወጥተው ለኅብረተሰቡ ትልቅ ጥቅም ሲሰጡ ይታያል። ነገር ግን በጥቅሉ ለሴቶች የመጫወቻ ሜዳው ሊስተካከል እና ሁሉንም እድሎች እንዲጠቀሙ መፍትሔዎች መቀየስ አለባቸው።

የተመድ የሴቶች አመራርነት እና ተሳትፎ ፕሮግራም የሴቶችን ውክልና ለማሳደግ የጀመረው ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት ይቀጥላል። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ሁሉም ዓይነት መድልኦዎች ለማስወገድ የተገባው ቃል ኪዳን ሴቶች በአደባባይ ሕይወት የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፤ የቤጂንግ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ደግሞ ሴቶችን እኩል ለመሳተፍ የሚያግዷቸው ጉዳዮች እንዲወገዱ ያትታል።

የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ሲፈተሹ ደግሞ የጾታ እኩልነትን ለማምጣት የተወሰዱ እርምጃዎች ሴቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ያላቸው የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ያመለክታሉ። የተመድ የሴቶች ፕሮግራም ይህንኑ ሂደት ለማስቀጠል ሴት የፖለቲካ ዕጩዎችን አቅም ይገነባል፣ የሲቪክ ትምህርት ይሰጣል ብሎም የሴቶች ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ይሠራል።    

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥታት እና ሌሎች አካላት እንዲሁ የሴቶችን አቅም ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ይወተውታል። በተጨማሪም ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የጾታ እኩልነት እንዲመጣ የሚያስችሉ እርምጃዎች ለፖሊሲ አውጭዎች ወሳኝ መሆናቸው ላይ በትኩረት እንዲሳተፉ የሚያበረታቱ ተግባራት ያከናውናል።

ሴቶች በሁሉም የፖለቲካ መስኮች ማለትም በመራጭነት፣ በዕጩነት፣ በተመራጭነት ብሎም የሲቪል ሰርቪስ አባላት እንዲሆኑ የሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ  ያበረታታል። በየሀገራቱ ከሚገኙ የተመድ አባላት እና ሲቪል ማኅበረሰቦች ጋር በመተባበር ሴቶች ያለ ምንም ውጣ ውረድ በመራጭነት እና በምረጡኝ ቅስቀሳ የመሳተፍ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ይንቀሳቀሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *