Skip to content

ትምራን ያዘጋጀችው የሴቶች የሰላም መድረክ በአፋር፣ ሰመራ ተጀመረ

በሴቶች በፖለቲካዊ እና በማንኛውም ሕዝባዊ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ውሳኔ ሰጪ የሆኑባት አትዮጵያን ማየት የሚል ራእይ አንግባ የምትንቀሳቀሰው ትምራን ያዘጋጀችው የሴቶች የሰላም መድረክ በአፋር፣ ሰመራ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክትትል እና ግምገማ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ሮቤል አበበ፣ ትምራን ኢትዮጵያውያን ሴቶች በማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን መብታቸውን እውን እንዲሆን እንዲሁም በአመራር ሰጭነት ሚናቸው እና አቅማቸው እንዲጎለብት የምትሠራ ነች ብለዋል።

አክለውም ትምራን ከሦስት ዓመት በፊት የተቋቋመች መንግሥታዊ ያልሆነች ተቋም መሆኗን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በሀገራዊ ምርጫ ወቅት ዋና፣ ዋና ጉዳዮችን ጨምሮ፣ ሴቷ ሰላምን ትምራ በሚለው ፕሮጀክቷ በተለያዩ ክልሎች የሰላም የእግር ጉዞ እንዲሁም የሰላም ውይይቶችን ስታካሂድ መቆየቷን ለመድረኩ ገልጸዋል።

በሰመራ ከተማ በመከናወን ላይ ያለው ውይይት ትልቅ ትርጉም ያለው እና የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎላ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመድረኩ ላይ የተገኙ የአፋር ክልል ሴቶች  በንቃት በመሳተፍ በሰላም ግንባታ ላይ ያሉ ችግሮችንና ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲያነሡ ጠይቀዋል።

የመድረኩ የክብር እንግዳ የሆኑት የአፋር ክልል የሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አሚና ሐሰን፣ በበኩላቸው ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው የአፋር ሴቶች የሰላም ጉዳይ የእኔ ነው በማለት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰላም ግንባታ የሴቶችን ሚና ለማጎልበት የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ሐሳቦች ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *