Skip to content

ትምራን ያዘጋጀችው ለሁለት ቀናት የሚቆይ የሴቶች ሰላም መድረክ በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ትምራን ኢትዮጵያውያን ሴቶች በማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን መብታቸው እውን እንዲሆን ብሎም ወደ አመራር ሰጭነት ደረጃ እንዲመጡ ለማድረግ የአቅም ማጎልበት ተግባራት የምታከናውን መሆኗን ተናግረዋል።

አክለውም ትምራን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመሳሳይ የሴቶች የሰላም መድረክ ማካሄዷን፣ ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በአመራርነት ላይ ያሉ ሴቶች ልምድ የማካፈል መድረክ ማካሄዷንና በተለያዩ የሞያ መስክ ለተሰማሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየሰጠች እንደሆነ ገልጸዋል።

የሰላም እጦት በዋናነት ሴቷ ላይ የጎላ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የሴቶች የሰላም መድረክ የተዘጋጀው ሴቶች የሰላም መሪ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል።

የትምራን ባልደረባ እና የመድረኩ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሮቤል አበበ በበኩላቸው ትምራን ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሰመራ (አፋር)፣ በጋምቤላ እና ሀዋሳ (ደ/ብ/ብ/ሕ ክልል) ተመሳሳይ የሴቶች የሰላም መድረክ  ማካሄዷን ጠቅሰዋል።

የሰላም መድረኩ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎላ ለውጥ ለማምጣት ያለመ እና ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ የክልሉ ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ያሉ ችግሮችንና ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ትምራን ሴቶች በፖለቲካዊ እና በማንኛውም ሕዝባዊ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ውሳኔ ሰጪ የሆኑባት አትዮጵያን ማየት የሚል ራእይ አንግባ የምትንቀሳቀስ ሀገር በቀል የተመዘገበች የሲቪክ ማኅበር ነች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *