Skip to content

ትምራን ያዘጋጀችው ለሁለት ቀናት የሚቆይ የሴቶች የሰላም መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ

ትምራን ያዘጋጀችው ለሁለት ቀናት የሚቆይ የሴቶች የሰላም መድረክ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ባልደረባ እና የመድረኩ አስተባባሪ አቶ ሮቤል አበበ፣ ትምራን ሴቶች በፖለቲካዊ እና በማንኛውም ሕዝባዊ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ውሳኔ ሰጪ የሆኑባት አትዮጵያን ማየት የሚል ራእይ አንግባ የምትንቀሳቀስ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር መሆኗን ተናግረዋል።

ትምራን ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ተመሳሳይ የሴቶች የሰላም መድረክ በሰመራ (አፋር)፣ ጋምቤላ እና ሀዋሳ ከተሞች ላይ ማካሄዷን አመልክተዋል።

ሰላም ሲናጋ በዋናነት ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሮቤል ይህ የሴቶች የሰላም መድረክ የተዘጋጀው ሴቶች የሰላም መሪ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ያለ ሴቶች ተሳትፎ በሰላም ጉዳይ ለውጥ ለማምጣት ስለማይቻል፣ የክልሉ ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል። የመድረኩ የክብር እንግዳ የሱማሌ ክልል ሴቶች ልማት ማኅበር ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ነቢሃ ጂብሪል በበኩላቸው፣ የክልሉ ሴቶች ሰላምን በተመለከተ በባለቤትነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *