
በትምራን አዘጋጅነት በጋምቤላ ከተማ የካቲት 01 እና 02 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደው የሴቶች የሰላም መድረክ ተጠናቀቀ።
በመድረኩ ሁለተኛ ቀን ውሎ ሴቶች ካለባቸው ተደራራቢ ቤተሰባዊ ሓላፊነት ጎን ለጎን ራሳቸውን ሊያበቁ እና ሊያነቃቁባቸው የሚችሉ መንገዶች በተመለከተ አሠልጣኟ ወ/ሮ ማኅደር ዳዲ ተሞክሮአቸውን ለተሳታፊዎች አካፍለዋል።
የጋምቤላ ክልል ሴቶች በሰላም ሂደት ለመሳተፍ መሰናክል የሚሆኑ ጉዳዮች በተመለከተ የባሕል ተፅዕኖ (የጎሳ አስተሳሰብ እና ሴቶችን ዝቅ ማድረግ)፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ተደማጭነት አላገኝም ብሎ መፍራት፣ የተመቻቸ መድረክ አለማግኘት የሚሉ ሐሳቦችን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ውይይት ላይ ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን ለማሳደግ እና ተፅዕኖ ለመፍጠር ሴቶች ራሳቸውን ብቁ ማድረግ፣ እርስ በእርስ መተጋገዝ እና በሰላም ዙሪያ ውይይት ማድረግ እንዲሁም መደራጀት እንዳለባቸው ተገልጿል።
በክልሉ ውስጥ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሴቶች የክልል፣ ወረዳ፣ ዞን እና ቀበሌ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ስለ ሰላም ውይይት ሥልጠና በመስጠት ብሎም ከሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት በማድረግ ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም የክልሉ ሴቶች ሰላም ግንባታ ውስጥ ሚጫወቱት ሚና ለማጎልበት በማኅበር መደራጀት፣ የሀብት ማሰባሰቢያ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ተጠቅሷል።
የጋምቤላ ክልል ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ስለ ሰላም በመስበክ፣ ወንዶች ወደ ግጭት እንዳይገቡ በማድረግ እና ዕውቀት በማጋራት ሊሳተፉ እንደሚችሉ ሐሳብ ተሰጥቷል።
ይህንንም እውን ለማድረግ የቤተሰብ ጫና የሚቀረፍበት ዘዴ ማፈላለግ፣ ፍርሃትን ለማስወገድ የሚረዱ ዘዴዎች መቀየስ፣ የወንዶችን አመለካከት ለመቀየር ጥረት ማድረግ እና በራስ መተማመን መፍጠር እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጭነት አቅም ለማሳደግ በዋናነት በምትሠራው ትምራን አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የሴቶች የሰላም መድረክ ላይ የማጠቃለያ ሐሳብ የሰጡት አቶ ሮቤል አበበ፣ ተሳታፊዎችንና ይህ ሥልጠና እውን እንዲሆን ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በማመስገን አጠናቅቀዋል።




