Skip to content

በጅግጅጋ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሴቶች የሰላም  መድረክ ተጠናቀቀ

በትምራን አዘጋጅነት በሶማሌ ክልል፣ ጅግጅጋ ከተማ የካቲት 16 እና 17 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሴቶች የሰላም መድረክ ተጠናቅቋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ሴቶች ከሰላም ጋር በተያያዘ በኢትዮ ቲንክ ታንክ አሠልጣኞች አማካኝነት ሴቶች በሰላም ሂደት እንዳይሳተፉ የሚያደርጋቸው ምንድነው? በሶማሌ ክልል ውስጥ ሰላም ለመገንባት ምን እየተከናወነ ነው? የሴቶች ሚናስ ምንድነው? የክልሉ ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማጎልበት ምን አዳዲስ ሂደቶች፣ ተቋማት እንዲሁም ሀብት ያስፈልጋል? ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ችሎታ ምንድነው? ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ ተዋናይ እንዲሆኑ ምን ዓይነት ስትራቴጂዎች መነደፍ አለባቸው? የሚሉ እና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ወስደዋል።

ተሳታፊዎች በየርእሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ የቡድን ውይይቶች ያካሄዱ ሲሆን፣ በሶማሌ ክልል ለሰላም እጦት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለው አንዱ ነበር።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከጉዳዪዩ ጋር በተያያዘ በርካታ ሐሳቦች ያነሡ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹ:-በከተማ መሬት ባለቤትነት ላይ በአንድ ቦታ ከሁለት በላይ ካርታ ወጥቶ መገኘት፣ የኑሮ ውድነት፣ የእርሻ እና የግጦሽ መሬት ይገባኛል ግጭት፣ በአካባቢው ተደጋጋሚ ረኃብ መከሰት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የቅጥር ሥራ ያላገኙ ወጣቶች መብዛት ፣  የሕግ አስከባሪ አካላት የዜጎች መብት ጥሰት ተባባሪ ሆነው መገኘት፣ የተካረረ የፖለቲካ ልዩነት መኖር፣ የዘራፊዎች መበራከት፣ የሴቶች መደፈር፣ የጎሳ ግጭት የሚሉትን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አስተባባሪው አቶ ሮቤል አበበ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ እሴት መሆኑን ጠቅሰው፣ ተሳታፊ ሴቶች በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሆነው እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል።

መድረኩን በማዘጋጀት ትምራን እንዲሁም የማቀናጀት ሥራውን ላከናወኑት የሶማሌ ክልል ሴቶች ማኅበር አመራሮች በተለይም ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ነቢሃ  ጅብሪል ብሎም በተለያየ መንገድ መድረኩ የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *