Skip to content

በትምራን አዘጋጅነት በጋምቤላ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሴቶች የሰላም መድረክ ቀጥሏል

በትምራን አዘጋጅነት በጋምቤላ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሴቶች የሰላም መድረክ ሁለተኛ ቀን ውሎ ቀጥሏል።

ሥልጠናው በኢትዮ ቲንክ ታንክ ግሩፕ አሠልጣኞች እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የቡድን ሥራዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በቡድ ውይይት ከተነሡት ርእሰ ጉዳዮች መካከል የሰላም ምንነት፣ የሰላም ዓይቶች፣ በጋምቤላ ክልል ለሰላም እጦት የሚሆኑ ምክንያቶች እና ውጤቶች፣ የሰላም ግንባታ እና ሴቶች፣ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ምንነት፣ ሴትነት እና ሰላም ያላቸው ዝምድና ይገኙበታል።

በዚሁ ውይይት ወቅት በጋምቤላ ክልል ውስጥ ለሰላም እጦት ምክንያት የሚሆኑ ብሔር፣ ጎሳ፣ ሥልጣን፣ መሬት፣ የግለሰብ ጠብ፣ ፖለቲካ፣ ቋንቋ፣ የሥራ ቅጥር አድልኦ እና ሙስና መሆናቸው ተጠቅሷል።

በጋምቤላ ክልል ሰላምን ለማስፈን ሴቶች የሚጫወቱት ሚና ጋር በተያያዘ አኙዋክ ማኅበረሰብ ውስጥ ዶን ካቸል (ሁላችንም በሰላም እንኑር) የሚል ጥበብ መኖሩ ተጠቅሷል። በተጨማሪም በአኙዋክ አዛውንት ሴቶች የሚመራ ጄይ የሚባል ሥርዓት እንዳለ ተወያየዮች ተናግረዋል።

ሴቶች እና ሰላም ጋር በተያያዘ ሦስት ንድፈ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ የጋምቤላ ክልል ሴቶች  በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ለሚኖራቸው ተሳትፎ እንቅፋቶች የሚሆኑ አንኳር ጉዳዮች በተሳታፊዎች ተለይተዋል።

ከእነዚህ መካከል በኑዌር ብሔረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ የፈለገውን ያህል ብትማር እና ብታውቅ ራስዋ ጎሳ ላይ ሥልጣን እንደማታገኝ እና ሥልጣን ልታገኝ የምትችለው በባል ጎሳ በኩል ብቻ እንደሆነ፣ ባል ከሌላት ደግሞ ወደ ስልጣን እንደማትመጣ ተጠቅሷል።

በክልሉ ውስጥ በሚከናወኑ የእርቅ ሂደቶች ላይ በወንዶች ስለሚገለሉ ሴቶች ቀጥታ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ተወያዮች አንሥተዋል።

እርቅ የሚከናወነው በጎሳ መሪዎች እና ሽማግሌዎች እንዲሁም ባለሥልጣናት አማካኝነት መሆኑንም የመድረኩ ተሳታፊ ሴቶች ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *