Skip to content

በትምራን አዘጋጅነት በሰመራ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሴቶች ሰላም መድረክ ተጠናቀቀ

በትምራን አዘጋጅነት በሰመራ ከተማ ጥር 15 እና 16 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደው የሴቶች ሰላም መድረክ  ተጠናቀቀ።

በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ምንነት፣ የሰላም ዓይቶች፣ የሰላም እጦት እና መዘዞች፣ የሰላም ግንባታ እና ሴቶች፣ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ምንነት፣ ሴትነት እና ሰላም በሚሉ ጉዳዮች ላይ በኢትዮ ቲንክ ታንክ ግሩፕ ገለጻ ተሰጥቷል።

ገለጻውን ተከትሎ በአፋር ክልል ውስጥ ሰላም የሚያሳጡ ምክንያቶች እና ውጤቶቹ ምን እንደሆኑ ከተሳታፊዎች ሐሳብ ተሰብስቧል። በክልሉ ሴቶች የሚሳተፉበት የሰላም ግንባታ ሂደት/ተቋም ስለ መኖሩ እና ሂደቱ ምን እንደሚመስል ተወያዮች ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የአፋር ሴቶች በሰላም ጉዳይ መሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ መንገዶች እንዲሁም እንዳይሳተፉ የሚያደርጉ መሰናክሎች በተመለከተ ተሳታፊዎች በቡድን ውይይት ለይተዋል።

ከመሰናክሎች መካከል ሴቶች የሥራ ክፍፍል ጫና ያለባቸው መሆኑ፣ ሴቶች ስለ ራሳቸው ችሎታ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በተለይም በገጠር አካባቢ አሁንም በስፋት የሚከናወን መሆኑ እና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል።

በክልሉ ውስጥ የሚተገበረው አብሱማ ተብሎ የሚታወቀው ባሕል ለግጭት ዋነኛ መንስኤ መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተነሥቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ሴቶች ፌደሬሽን ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አሚና ሁሴን በክልሉ ውስጥ ሴቶች በሽምግልና ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ፣ ግጭት ሲነሣ የማስታረቅ ሚና እንደሚጫወቱ እና የግጭቱ ምክንያት ውስብስብ ሲሆን ለጎሳ መሪ በማሳወቅ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ፎረሞች እና ማኅበራት ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ተመላክቷል። በመሆኑም የፋይናንስ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ሊደረጉላቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ባቀረቧቸው ሐሳቦች መሠረት ሀገራዊ የሰላም ግንባታ ስልት (ስትራቴጂ) ቀርቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *