በትምራን አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ ሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት የተዘጋጀ ለአራት ቀናት የሚቆይ የፖለቲካ ተግባቦት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ሥልጠና የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዚማን ሆቴል ተጀመረ።
በሥልጠናው ላይ ተሳታፊዎችን እንኳን ደኅና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ትምራን የዛሬ ሦስት ዓመት ተቋቁማ በአጭር ጊዜ በርካታ ሥራዎች መሥራት የቻለች ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር መሆኗን ጠቅሰው፣ ከ50 በላይ የሲቪክ ማኅበራት ያቀፈው የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሴክሬታሪያት በመሆን እያገለገለች መሆኗን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት ለአራት ቀናት የተዘጋጀው የፖለቲካ ተግባቦት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ሥልጠና ከየፖለቲካ ፓርቲዎች በተሰበሰበ ግብአት መሠረት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ከሁለት ሳምንት በፊት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ለጥምረቱ አባላት በፖለቲካ ውስጥ ያለ የጾታ ጥቃት በተመለከተ በዋናነት ወንዶችን ያሳተፈ ሥልጠና ትምራን መስጠቷን ጠቅሰዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጇ ትምራን አቅማቸው የተገነባ እና በፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ያላቸው ሴቶች የመፍጠር ራእይ ይዛ የምትሠራ የሲቪክ ማኅበር መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህንን የፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ሥልጠና ማዘጋጀቷን ተናግረዋል።
የሥልጠናው የክብር እንግዳ የሆኑት የሥራ እና ክሂሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ነቢሃ መሐመድ፣ ትምራን በተለያዩ ጊዜያት ሴቶች ያላቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና በመስጠት ትልቅ ሥራ እያከናወነች ያለች መሆኗን ተናግረዋል።
ትምራን ያዘጋጀችው የፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ሥልጠና የሴት ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ጥምረት ፍላጎት መነሻ በማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አሁንም ድረስ ውስን መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ይህንን ለመለወጥ በየተወከልንበት ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ብዙ መሥራት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ተሳታፊዎች ሌሎችን ለማብቃት ሥልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።