Skip to content

ሴቶች እና የሰላም ግንባታ

ሴቶች የለውጥ ሐዋርያ ለመሆን የሚያስችል ድምፅ እና አቅም አላቸው። በየአካባቢዎች በሚደረጉ ውይይቶች፣ የተሻሉ ፖሊሲዎች እና ፍትሐዊ የሰላም ስምምነቶችን ለማምጣት ለጾታ ጉዳይ ትኩረት መስጠት እና የሴቶችን ተሳትፎ፣ ድምፅ እና አቅማቸውን መጠቀም ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ዘላቂነት ያላቸው፣ ሰላማዊ መስተጋብሮችንና የአስተዳደር ዓይነቶችን ብሎም መዋቅሮችን እውን ለማድረግ የሰላም ግንባታ የተሟሉ አቀራረቦች፣ ሂደቶች እና ደረጃዎችን ያልፋል። በተጨማሪም ሕጋዊ እና የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እንዲሁም ፍትሐዊ እና ውጤታማ አስተዳደር እና ግጭቶችን የመፍታት ሂደቶች እና ሥርዓቶች ያካትታል።

በግጭት ወቅት በዋናነት የሚፈናቀሉት ሴቶች መሆናቸው ይታወቃል፤ ይህም ሴቶች ግጭትን ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ያሳያል። ሲልቨስተር የተባለ ተመራማሪ የአቴና ሴቶችን “ሰላምን የሚወዱ ውብ ነፍሶች” ሲል ይገልጻቸዋል። ይህም በሴቶች መብት ንቅናቄ ጥናት ውስጥ ሴቶች በተፈጥሮ ሰላማዊ፣ ስለ ሰላም መስበክ፣ ማስተማር ብሎም መጠበቅ የሚችሉ መሆናቸውን ከሚገልጸው ንድፈ ሐሳብ ጋር የሚጣጣም ነው።

ቦቢት እና ፒርሰን በተባሉ አጥኚዎች የተከናወነ ጥናት እንዲሁ ግጭትን ለመፍታት በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች ላይ ሴቶችን ብቻ ያካተቱ ቡድኖች ውስጥ ቅልቅል ጾታ ካላቸው ቡድኖች በተሻለ መልኩ ገንቢ ውይይቶች እንደሚደረግ አረጋግጧል። ይህም ሴቶች ሓላፊነት የሚሰጣቸው፣ የሚተማመኑባቸው እና ከፍተኛ እምነት እና ተግባር የሚጣልባቸው ናቸው ከሚለው አስተምህሮ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ይህም ሴቶች ቁርጠኛ፣ እምነት የሚጣልባቸው እንዲሁም ለቤተሰባቸው እና ለሀገራዊ ፍላጎቶች እና ግቦች ራሳቸውን የሚሰጡ መሆናቸውን ያሳያል።

ፌሪስ የተባለ ተመራማሪ እንዲሁ ሴቶች ግጭቶችን በመፍታት ሂደት ውስጥ በሚያጋጥማቸው ውጣ ውረድ አልያም ማስፈራሪያ የተነሣ ጉዳዩን ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ ቢሆንም፣ እስካሁን ያላቸው ሚና የሚገባውን ያህል ተቀባይነት አልያም እውቅና እንዳልተሰጠው አትቷል።

ሴቶች የተለያዩ ቡድኖች የማንነት አጥራቸውን ሰብረው በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት መፍታት እንዲችሉ መንገድ ጠራጊ ናቸው። ስለሆነም ሴቶች እና ሰላምን አስመልክቶ የሚደረጉ ውይይቶች ቁጥሮች ላይ ማለትም “ሴቶችን ማካተት እና መጨመር” የሚለውን ሐሳብ ብቻ የሚያይ መሆን የለበትም። ይልቁንም በሰላም ግንባታ ተቋማት የውሳኔ ሰጭነት ደረጃዎች ላይ “ብዙ ሴቶችን ማካተት” ወሳኝ የመነሻ እርምጃ መሆኑን ያሳያል። ትልቁ ተግዳሮት ያለውም የወንዶችንና የሴቶችን እይታ ያካተተ የማይዛነፍ ሰላም እና ደኅንነት መገንባት እና አብሮ መኖር፣ ብጥብጥን መግታት እና አካታችነት የሚሉ እሴቶችን ማምጣት ላይ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *